ለህዝቦች ማንነት፣ ለባህላቸው፣ ለታሪካቸውም ሆነ ለቋንቋቸው ከበሬታ እና እድገት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና በመስጠት ይህንኑ ለማስፈፀም በወጣው ሀገር አቀፍ የባህል ፖሊሲ መሰረት በየደረጃው የህብረተሰቡን ኪነ-ጥበባዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያስችሉ የባህል ተቋማት መመስረትና መስፋፋት እንዳለባቸው በመታመኑ፣ በተፈጠረው መልካም ዕድልም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳደር ም/ቤት በአዋጅ ቁጥር 24/96 ደንብ ወጥቶለት እና ለህዝቡ ባህላዊ እሴት ግንባታ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ይሆን ዘንድ በማሰብ እና በክልሉ የባህል ማዕከል መቋቋም አስፈላጊ መሆኑ በመታመኑ ሙሉዓለም የባህል ማዕከልየሚል ስያሜ ተሰጥቶት ተቋቋመ፡፡
በክልሉ ርዕሰ ከተማ በሆነችው ባህር ዳር ከተማ በሰኔ ወር 1987 ዓ/ም የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታዉ ከተጠናቀቀ በኋላ ጥቅምት 4/1990 ዓ/ም ተመርቆ መንግስታዊ መስሪያ ቤት በመሆን ስራውን በይፋ ጀመረ፡፡ ባህል ማዕከሉ በዋናነት ስያሜውን ያገኘው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ጎንደር ዞን በድሮዉ ፀዳ ወረዳ አንቦበር ቀበሌ ልዩ ስሙ ዉዝባ በሚባል ቦታ በ1952 ዓ/ም ይችን ዓለም ከተቀላቀለዉ “አዳነ ስብሀት ሰንደቄ” በማለት ቤተሰቦቹ ስያሜ ካወጡለት እና በ1970 ዓ/ም በ18 ዓመቱ ከብአዴን የትግል ጓዶች ጋር ወደ ትግል ሲገባ “ሙሉዓለም አበበ” የሚል የትግል መጠሪያን ስም የተሰጠዉን የታጋይ ሙሉዓለም አበበ ስምን በመያዝ ነዉ ባህል ማዕከሉ በመጠሪያነት የሚጠቀመዉ፡፡
በመሆኑም ታጋይ ሙሉዓለም አበበ ለኪነ-ጥበብ በነበረዉ ከፍተኛ ፍቅርና ጥልቅ ስሜት ሙሉዓለም የባህል ማዕከል መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በስሙ ሊሰየም ችሏል፡፡