አድርሽኝ ጎንደር እና ሀገረሰባዊ ዜማዉ! በገብረማርያም ይርጋ አለማየሁ ጎንደር በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ከአክሱምና ላሊበላ ቀጥሎ ትልቋ የመንግስት ማዕከል ነበረች፡፡በመንግስት ማዕከልነት የተቆረቆረችዉ በአጼ ፋሲል (1624-1660ዓ.ም) ነዉ፡፡ ጎንደር የመንግሥት ማዕከል ብቻ ሳትሆን በጊዜው የመንፈሳዊ ትምህርት ማዕከልም ነበረች፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመጻሕፍት እና የአቋቋም ትምህርት ይበልጥ የተስፋፋውና በየሀገሩ ያሉ ሊቃውንት በመናገሻ ከተማዋ ጎንደር በነገሥታቱ አማካይነት በመሰባሰባቸው ሲሆን ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ መንፈሳዊ ትምህርት በስፋት የሚሰጥባት የትምህርት ማዕከል ለመሆን ችላለች፡፡ ጎንደር የመንግሥት ከተማ ከሆነችበት እስከ ጎንደር ዘመን ማክተሚያ ፍፃሜ መንግሥት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ (1772-1777) ድረስ 18 ነገሥታት የነገሱ ሲሆን ከእነዚህ ነገስታት መካከል ንጉስ አፄ ዮስጦስ (1703-1708) አንዱ ናቸዉ፡፡ ንጉስ አፄ ዮስጦስ በ ዙፋን ዘመናቸው ተቀናቃኝ በዝቶባቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በሐምሌ ክረምት ከተነሳባቸው ክፉ ተቀናቃኝ ጋር ለሰልፍ ከመውጣታቸው በፊት ወደ ታቦተ ልደታ መጡና ‹‹የፍልሰታ ፆም መጣልኝ እያልኩ ቀን ስቆጥር ክፉ ጠላት ተነስቶብኛል፡፡ ልጂሽ ወዳጂሽ በሰልፌ እንዲቆም ተማፅኛለሁ፡፡ ስዕለቴ ሰምሮ ተመልሸ ሱባኤሽን በደጅሽ እንዳሳልፍ ካደረግሽኝ በየዕለቱ ዝክርሽን እዘክራለሁ፡፡ ሲሉ ተሳሉ፡፡ ሰምሮላቸው ለፆመ ፍልሰታ በአጸዷ ተገኙ፡፡ ለፆም እንደሚገባ ብቁልትና አሹቅ አዘጋጅተው ጠላ አስጠምቀው፣ ከቅዳሴ መልስ ካህናቱንና ህዝቡን አድርሽኝ አልኳት አደረሰችኝ እያሉ መዘከር ጀመሩ፡፡ ይህ ግብርም አድርሽኝ ተባለ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አድርሽኝ በፍልሰታ ጾም ወቅት የሚካሄድ እመቤታችን ድንግል ማርያም እንኳን አደረሽን በማለት ለተማጽኖ እና ምስጋና በየአመቱ ከነሀሴ አንድ እስከ ነሀሴ 16 በጎንደር ማህበረሰብ በቤት ውስጥ እና በሰንበት ትምህርት ቤት የሚከወን ሀይማኖታዊና ማህበረ ባህላዊ ስርዓተ ከበራ ነዉ፡፡ ከበራ የእምነት ስርዓት ነዉ፡፡ እምነት ካለ ምስጋና ወይም ተማጽኖ መኖሩ አይቀርም፡፡ ምስጋናም ሆነ ልመና ያለ እንጉርጉሮ፣ዜማ አይታሰቡም፡፡ ምስጋናም ሆነ ልመናዉ፣ እንጉርጉሮ፣ዜማዉ ደግሞ የማህበረሰቡ/ ሀገረሰባዊ ዜማ ነዉ፡፡ ሀገረሰባዊ ዜማ/ ሙዚቃ በታሪክና በባህል ሁነቶች፣ በእምነት፣ የስራ ባህልን ተከትሎ የተፈጠረና ከተለያዩ ባህሎች እየተወራረሰ፣ በታሪክ ሂደቶች እያለፈ፣ በተለያዩ ሁኔታዎች እየተወሰነ የመጣ በማለት ይገልፃል፣ (Bohlman, 1988) ፡፡ ሰዎች ወደፊት ይገጥሙናል ብለው የሚያስቧቸውን ነገሮች መልካም ለማድረግ፣ መጥፎዎችን እንዳይከሰቱ ለመከላከል፣ ከጭንቀት ለማምለጥ፣ ሃብት ንብረታቸውን ለመጠበቅ፣ የተወለደው ይባረክ፣ የተዘራው ይመረት ዘንድ ለመለማመን ሲሉ በሚያበጁት መንፈሳዊ መስተጋብር ሙዚቃ መፈጠሩን፤ በዚህ መስተጋብር እምነት መነሻ መሆኑን፣ በተለያዩ ሁኔታዎች ፣በታሪክ ሂደቶች ሀገረሰባዊ ዜማዉ እየተፈጠረና እየተወራረሰ መምጣቱን እንገነዘባለን፡፡ ሃገረሰባዊ ዜማ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል የሚተላለፍ እንደመሆኑ ማህበረሰቡ ዝማሬዉን የሚማረውም ሆነ የሚተውነው ካለፈው ትውልድ በቃል በማስታወስ ነው፡፡ ዜማዉን የማህበረሰቡ ህይወት በመሆኑ አድማጩ ሳይቀር ከዋኙ በትክክል መከወኑንና አለመከወኑን ካለው ሃገረሰባዊ የሙዚቃ ዕውቀት ተነስቶ ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ በማህበረሰቡ ዉስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየ፣ ሀገር በቀል የዜማ ስልትን ተጠቅሞ፣ባህላዊ የድምጽ ቃናን መሰረት በማድረግ ፣የማህበረሰቡን ባህል በሚያንጸባርቁ ተመሳሳይ ዜማዊ ቅርጾች ውስጥ የሚገኝ በቃል የሚዜም ነዉ፡፡ ማንኛውም ማህበረሰብ ከሌሎች ማህበረሰቦች የሚለየው እንዲሁም ከሌሎች ማህበረሰቦች የሚጋራው ወግና ልማድ ይኖረዋል። የጎንደር ማህበረሰብም ከሌሎች ማህበረሰቦች የሚጋራቸውና የራሱ የሆኑ ሀዘኑንና ደስታውን የሚገልጽባቸው፣ እምቱን፣ባህሉን፣እሳቤዉን የሚያደምቅባቸው፣ ፍልስፍናዉን የሚያንጸባርቁ ጥልቅ ስሜቶችን የተሸከሙ ክዋኔዎች አሉት። በአድርሽኝ ከበራ ወቅት ከሚከወኑት ፎክሎሮች መካከል “ሆ ማርያም” በመባል የሚከወነዉ ሀገረሰባዊ ዝማሬ/ዜማ አንዱ ነዉ ። …ግጥም 1… ኦ ማርያም እለምንሻለሁ ባሪያሽ፤ አንድ ጊዜ ስሚኝ ቀርበሽ ከአጠገቤ ቆመሽ፤ ፅኑ ጉዳይ አለኝ ላንቺ የምነግርሽ፤ የዓለምን መከራ ያየሽ፤ በእናት በአባችሽ ሀገር፤ሄሮድስ አስከድቶ ሰዶሽ፤ በምድረ ግብፅ ዞረሽ ውሃ የለመንሽ ከልጅሽ አማልጅኝ ድንግል ልመናየ ይሆናል ብለሽ፤ በላኤ ሰብን አንችኮ ነሽ ያስማርሽ፤ ሆ ቸሪት ተመላለሽ ሌሊት በህልሜ ቀርበሽ፤ አደራሽን እጀን በእጅሽ ያዣት እንዳልባክን፤ አደራሽን የመጣሁ ቀን አስምሪያት ነፍሴን፤ ማሪኝ በደሙ ለኛ ብሎ ልጅሽ በፈሰሰ ደሙ/2/ ******** ይህ ቃል ግጥም በመንፈሳዊ ሃገረሰባዊ ዜማዉ ክዋኔ መጀመሪያ ላይ የሚባል ሲሆን ማህበረሰቡ ከአፈ ታሪኩ በመነሳት ለማርያም ባዘጋጀው የምስጋና እና የልመና ክዋኔ ላይ ቀርባ አላማውን ትፈጽምለት ዘንድ ቀርበሽ ስሚኝ ማርያም ሆይ ሲል አደራዉን ያቀርብላታል፡፡ ቃል ግጥሙ በስርዓተ ክዋኔዉ ላይ ለማርያም ልመና በማቅረብ እንድትሰማቸዉ፣ እንድታስምራቸዉ ለመለመን የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ማርያም ቸል የማትል እንደ ልጇ የለመኗትን የማትረሳ የጠየቋትን የማትነሳ መሆኗን አምነው ያደሩ አማንያን አበክረው አንገታቸውን አቀርቅረው ዕንባዋን ተውሰው ፊታቸውን በእንባ ዘለላ ሸፍነው ″ኦ ማርያም እለምንሻለሁ ባሪያሽ″ እያሉ ራሳቸውን ለማርያም ቅሩብ አድርገው ይማፀኗታል፡፡ በእናት በአባችሽ ሀገር ሄሮድስ አስከድቶ ሰዶሽ፤ በምድረ ግብፅ ዞረሽ ውሃ የለመንሽ፡፡ የሚሉት ስንኞች በሀገረ ግብፅ የደረሰባትን እንግልትና ስደት ምሉዕ በኩለሔውን ልጇና አምላኳን በጉያዋ ደብቃ ግን ውሃ ጥም ከሰው ደጅ አቆማት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ″ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል″ እንዲል (ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፤17) በእርሱ ለእርሱ የተፈጠረው ራሱ በሰራው ፍጡር ውሃ ተጠማ፡፡ የእናቱን ጉሮሮ የሚያርስ እፍኝ ውሃን ሳያጠፋው ጠፍቶ የምድር የሰማይ ንጉስን የተሸከመችው ርህርህት እናቱ በየሰው ደጅ ውሃ ስጡኝ እያለች ባዘነች፡፡ ″ከልጅሽ አማልጅኝ ድንግል ልመናየ ይሆናል ብለሽ…″ ስለዚህ የዓለሙን መከራ በጥልቀት ያየሽው የተረዳሽው በምድረ በዳ የተንከራተትሽው ስደተኛዋ ማርያም እኛም በዓለም ፈተና እንዳንዳረግ ከምጥ ከጣረሞት እንዲሰውረን ከልጅሽ ደጅ አድርሺልን ሲሉ ቃለ ምልጃቸውን በእንዲህ አይነቱ ቃለ ግጥም ያቀርባሉ፡፡ በላኤ ሰብን አንችኮ ነሽ ያስማርሽ፤ ሆ ቸሪት ! ተመላለሽ በህልሜ ቀርበሽ፤ ከዚህ ተነስተው ከልጅሽ አማልጅኝ ድንግል ልመናየ ይሆናል ብለሽ እያሉ 78 ሰዎችን ቀርጥፎ የበላ የቀደመ ስሙ ስምዖን ኃለኛው ስሙ በላዔ ሰብዕ ወይንም ሰው በላው ሰው በበርሀ ቀማኛ ሆኖ ሳለ የሰው ልጅን ስጋ ክፉ ልክፍት ሆኖበት ብዙ ዘመናትን የቆየ ክፉ ወንበዴ የነበረ ሲሆን ከዕለታት በአንድ ቀን ግን በበርሀ ሳለ አንድ እጁ ቁምጥና ያለበት ሰው ውሃ ጥሙን እንዲያስታግስለት የቸሪቷን ማርያም ስሟን ጠርቶ ሰው በላውን ሰው ጥርኝ ውሀ ከድኩም መዳፉ ላይ እንዲያፈስለት ማለደው፡፡ ሰው በላው ሰውም ያንን ሰው በያዘው ሰይፍ ግዳይ ጥሎ ሸልቶ ከመመገብ ይልቅ ከአንደበቱ የወጣችውን ለወትሮው ስሟ ሲጠራ የሚጣፍጠውን የማርያም ስም ሲጠራ ከልቡ ራራ፡፡ የያዘውን የውሀ መያዣ መንቀል አውርዶ ከመዳፉ ላይ አፈሰሰ፡፡ በዚህም የተነሳ ነፍሱ በአምላኳ ፊት ቀርባ ተማረች፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት እንዲህ እንዲል ″ለችግረኛ ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፣ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋልና″ መዝሙር 40፤1 ለቃሉ ሐሰት በሌለበት ልጇ ወዳጇ ስምሽን ጠርቶ ለዘከረ ምህረትን አደርጋለሁ ባለው ቃል ኪዳኑ መሰረት በላዔ ሰብን በጥርኝ ውሃ ራሮት በምህረቱ ገነት የመግባት ዕድል አቀዳጀው፡፡ ስለዚህ እኔንም ቸሯ የአምላክ እናት ቀርበሽ የመማር ህልሜን የበላዔሰብን በጎ ዕጣ አድይኝ በሚል ቃለ ግጥም ለሐጢዓት ስርየት ልባቸውን ለዜማ አነቁት፡፡ እንኳን ለፆመ ፍልሰታ አደረሳችሁ! ማስታወሻ፡- ለ2ኛ ድግሪ መመረቂያ ካጠናሁት የተወሰደ መሆኑን እየገለጽኩ፤የአድርሽኝ ከበራ እና ‹‹የሆ ማርያም›› ክዋኔ ልማድ (አዉዱ) የበለጠ እንዲታወቅና እንደ አንድ መስህብ አንዲታይ፣ ጎልቶ እንዲወጣ የአካባቢዉና የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ተቋም የማስተዋወቅ ስራ ቢሰሩ፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ክዋኔዉ ያለዉን መንፈሳዊና የአዕምሮ እርካታ ፋይዳ ቢያጎሉት፣ ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ፋይዳ ይበልጥ ቢጠና ለማለት እወዳለሁ!፡፡
ይቀጥላል….