ሙሉዓለም የአማራ ባህልና ኪነ-ጥበባት ማዕከል ተተኪ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞችን ለማፍራት ስልጠና እየሰጠ ነዉ፡፡
በማዕከሉ ትውን ጥበባት ጥናትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በሙዚቃም ሆነ በቴአትር ዘርፍ ተተኪ የኪነ-ጥበብ ከያኒያንን ለማፍራት የሚያስችል፣ ክፍተት የለየና አቅምን ሊያጎለብት የሚችል ተግባራዊ ስልጠና ከሐምሌ 18/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
የዳይሬክቶሬቱ የትያትርና የሙዚቃ ስልጠና ቡድን አስተባባሪ ወ/ት ትግስት ማሩ እንደተናገሩት ስልጠናዉ በዚህ ጊዜ መሰጠቱ በርካታ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ተዳጊ ወጣቶች ከትምርት ነፃ ሆነዉ የሚያሳልፉበት ጊዜ በመሆኑ ጊዜቸዉን ሳያባክኑ በአግባቡ በመጠቀም በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ አዳዲስ እዉቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡
በዘርፉ እየሰሩ ያሉ ተተኪ ከያኒያን ከአሁን በፊት በልምድ ከሚሰሩ መንገድ በተሻለ በተግባር ልምምድና ሳይንሳዊ ገለፃ ታክሎበት ስለሚሰጥ ሙያዉ ከፍ እንዲል ያደርጋል ያሉት ወ/ሪት ትግስት ሰልጣኖችን ለቀጣይ ስራቸዉ ሙያቸዉን ከፍ በማድረግና በማጎልበት የሚጠቀሙበት ስልጠና መሆን አያይዘዉ አስረድተዋል፡፡
ማዕከሉ ለሰልጣኞች የሚሠጣቸዉ የስልጠና ዘርፎችም በትያትር ዘርፍ በጽህፈተ ተዉኔት፣ በትወና ሙያ፣በዝግጅት እንዲሁም በሙዚቃ ዘርፍ በባህላዊ ዉዝዋዜ፣በድምጽ፣ በመሰረታዊ የሙዚቃ ፅንሰ ሀሳብ እና በባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ አጨዋወት ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን በአጠቃላይ 293 ሰልጣኞች በስልጠናዉ በመሳተፍ እንደሚገኙ ከማዕከሉ ትውን ጥበባት ጥናት ስልጠና ዳይሬክቶሬት ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል ፡፡
ተተኪ የኪነጥበብ ሙያተኞችን ለማፍራት ስልጠና ወሳኝ ነው!!
ዛሬ የምንሰራዉ የነገ ታሪካችን ነዉ!!
ሙሉዓለም የአማራ ባህልና ከኪነ-ጥበባት ማዕከል!!
ሐምሌ 29/2014 ዓ.ም
ባህር ዳር